የክረምት ችግኝ ተከላ ዘመቻ በይፋ ተጀመረ
- WE+ Etyhiopia
- Jul 20, 2018
- 2 min read

አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2010 የዘንድሮው የክረምት ችግኝ ተከላ ፕሮግራም አንድ ችግኝ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ዘመቻው የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጋር በመሆን በሰበታ ከተማ አዋስ ቀበሌ በዛሬው እለት ባካሄዱት ችግኝ ተከላ ተከፍቷል።
በዚሁ ወቅት በተላለፈው መልዕክት ህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ባህሉን አዳብሮ ሊቀጥል እንደሚገና ከመትከል በዘለለም እድገቱንም እንዲከታተል ጥሪ ተላልፏል።
በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የደን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ይማም የዘንድሮው ችግኝ ተከላ ካለፉት ጊዜያት በተለየ መልኩ ከተከላ ባለፈ እንክብካቤ ላይ የተሻለ ስራ ለመስራት የታቀደበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት ባለፉት አመታት ብዙ ችግኞች በብዙ ገንዘብና ጉልበት ቢተከሉም የሚያገኙት እንክብካቤ አናሳ በመሆኑ እኩሌታ የሚሆኑት ሳይፀድቁ ይቀራሉ ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታትና ህብረተሰቡ የተከለውን ችግኝ ተንከባክቦ ለማሳደግ እንዲችል ከክልል አመራሮች ጋር በውይይት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ከስምምነቱ መካከል የግልና የጋራ ባዶ ቦታዎች ላይ ችግኝ ለሚተክሉ አካላት ሰርተፊኬት መስጠትን ያካተተ ነው ያሉት።
በዚህ ዓመት በአገር ደረጃ አራት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታሰበ ሲሆን እስካሁን በሁሉም ክልሎች ሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ችግኝ ለተከላ ዝግጁ ሁኗል።
ቁምነገሩ ችግኝን መትከል ሳይሆን ጥራትን ማዕከል ያደረገ ተከላና እንክብካቤ መኖሩ ላይ ያለ መሆኑንም አሳውቀዋል።
በችግኝ ተከላ አፈርን ማቀብ ሲቻል ታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ግድቦችን በደለል የመሞላት ስጋታቸውን ከመቀነስ አልፎ ለግብርናውና ለውሃ ክምችት ማደግ አስተዋፅኦው የጎላ ይሆናልም ብለዋል።
በአገሪቷ አሁን ላይ ከሚተከሉ ችግኞች ይበልጥ የሚቆረጡ ደኖች መቶኛ የበዛ በመሆኑ የችግኝ ተከላው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ፕሮግራሙን በይፋ ያስጀመሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ የችግኝ ተከላው አገርን ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ለመከላከል እንደሚያስችል በመጥቀስ ህብረተሰቡ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ህብረተሰቡ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እስካሁን የድርሻውን እየተወጣ ሲሆን የግድቡ ስጋት ሊሆን የሚችለውንም የደለል ስጋት ችግኝን መትከል ቢያክልበት የግድቡን የአገልግሎት እድሜ ማራዘም ይቻላል ብለዋል።
በተደረጉ የደን ተከላ ስራዎች አገሪቷ የነበራትን የደን ሽፋን ከሶስት በመቶ ወደ አስራ አንድ በመቶ ማድረስ ቢቻልም አሁንም የደን ጭፍጨፋ መኖሩን ጠቁመዋል።
ለማገዶና ለተለያዩ ስራዎች የሚጨፈጨፈውን ደን ለመቀነስ ታዳሽ ኃይልና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ገልፀዋል።
እስካሁን በተሰራው ስራም አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በፈቃደኝነት በአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች ላይ በመሰማራት ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል።
Comments